ከዶክተር ምህረት አንደበት የተጨመቁ ጠቃሚ ንግግሮች

........ጥረህ ግረህ ብላ ብሎ መፅሓፍ ቅዱስ እውነታውን አስቀምጦልን፣ እኛ ግን በቀላሉ መኖር የሚል የህይወት ፍልስፍና ውስጥ ስንገባ ነው ነገር ዓለሙ የተበላሸው። እኛ ከማንም በፊት ብረት የቀጠቀጥን፣ የቆዳ ማልፋት የሰራን፣ ሸምነን የለበስን፣ ሌላም የእጅ ሥራ ውጤቶችን ፈጥረን ለውጤት ያበቃን ነበርን። ለምን ይሄ ሁሉ ቆመ? ለምንድነው ብረት ከውጪ ማስገባት የጀመርነው? ለምንድነው የእኛ ሸክላ በፕላስቲክ የተተካው? ይሄ እኮ የአመለካከት ድክመት ያመጣው ነው። በቀላሉ መኖር ስንጀምር በራሳችን ፈጠራ ማደጉ የሆነ ቦታ ተገታ። እንዴት ነው ሰው ሳይሰራና ሳይደክም ዕድገትን በባዶ ሜዳ የሚያልመው? እኛ ከሌሎቹ ሕዝቦች በምን እናንሳለን? እነሱም ሰዎች እኛም ሰዎች ነን፣ ፈጣሪ ለእኛም ለእነሱም እኩል የማሰቢያ ጭንቅላት ሰጥቶናል። አሳንሶም፣ አስበልጦም አልፈጠረኝም። ሌላው በተሰጠው ከሰራበት እኔም በተሰጠኝ መስራት እና ለውጥ መፍጠር አለብኝ ብሎ ራስን ማሳመን አለብን።
......." አንድ ካሬ ሜትር መርካቶ ውስጥ 350 ሺ ብር ካወጣና አንድ ፕሮፌሰር አርባ አመት ደክሞ በወር የሚያገኛት የአንዲት ካሬ ሜትር ዋጋ የምትመዝን ካልሆነች ሰው ተፈጥሮን አላሸነፈውም ማለት ነው፣ ሰው ከተፈጥሮ አልበለጠም ማለት ነው። መሬት ተፈጥሯዊ ነች፣ ለምንድነው ትንሿ መሬት ይህቺን ያህል ስትወደድ ለምንድነው እኛ ይሄን ያህል አመት የተማርን ሰዎች ልንወደድ ያልቻልነው? ምክንያቱም በምንፈታው ችግር ልክ ነው እኛ ልንወደድ የምንችለው!! መሬቷ 30 ፎቅ ስለሚሰራባት 30 ፎቅ ልትከራይ ነው። የዚያች ቁራሽ መሬት ዋጋ ወደ ላይ 30 ፎቅ ሲያሰራ፣ እኛ ግን አንዲት ክፍል ውስጥ ገብተን ነው የምናስተምረው!!....የእኛ 30 እና 40 አመት የተማርንበት ዋጋ ግን ለብዙ ትውልድ መትረፍ አልቻለም። መብራት አልሰራም፣ አውሮፕላን አልሰራም፣ መርከብ አልሰራም፣ ባቡር አልሰራም። ሲንጋፖር ዕኮ መሬት የላትም! የምትሸጠው ዕኮ የአዕምሮዋን ውጤት ነው። የአዕምሮዋ ውጤት ደግሞ በአመት 540 ቢሊዮን ዶላር$ ኤክስፖርት ወደውጪ ይደረጋል። የእኛ የተፈጥሮ የሆነች ነገር ደግሞ 100 ሚሊየን ሕዝብ ይዘን የምታመጣልን 3 ቢሊየን ያልሞላ ኤክስፖርት እናደርጋለን። ሲንጋፖር 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሕዝብ የያዘች ትንሽ ሀገር ናት። ስለዚህ አዕምሮ መስራት ካልቻለ የተፈጥሮ መሬት የበለጠ እየተወደደች ትሄዳለች። እናም መማር ችግር ፈቺነትን ካላሳደገ፣ አዕምሯችን የተሻለ ነገር መፍጠር ካልቻለ፣ መሬት ላይ ቤት ሰርቶ፣ አከራይቶ፣ ሽጦና ለውጦ የተፈጥሮን ነገር ብቻ ሙጥኝ ብሎ መገላበጡ ይቀጥላል።
...."በእርግጥ በአዲስ ራዕይ እየሮጡ ያሉ ብዙ ወጣቶች አሉ። እኔ እንኳን በግል የማውቀው አንድ የ26 አመት ዕድሜ ያለው ወጣት አለ። ይሄ ወጣት በዚህ ዕድሜው ከተማ ውስጥ ትላልቅ ሕንፃዎች አሉት። ሰፋፊ የቡና እርሻዎች አሉት፣ የማዕድን ውሃ የሚያመርት ፋብሪካ አለው፣ ቢዝነስን የጀመረው ገና በ12 አመቱ ነው። He is Running እንዲህ አይነት የማውቃቸው ጥቂት ይሁኑ እንጂ በጣም ዳይናሚክ የሆኑና ነገ ሞዴል ሊሆኑ የሚችሉ ማሳያ ወጣቶች አሉን። ይሄ ትውልድ ላይ አሉታዊ ነገር እንዳለ ሁሉ ልናስቆማቸው የማንችላቸውም ምርጥ ወጣቶች እያየን ነው። ልንቆልፍባቸው ብንልም በየትኛውም ዘርፍ የማይቆለፉልን ልጆች እያፈራን ያለበትም ሁኔታ ታዝቤያለው። የወደቀው ወድቋል፣ ከዚህ በኋላ ግን የሚወድቀው ቁጥር እየቀነሰ የሚመጣ ይመስለኛል፣ ተስፋም አደርጋለሁ።
...." ሀብትን በአቋራጭ የማግኘት ምኞቱና ፍላጎቱ የሀገራችን ችግር ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ነው። ይሄ 99 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ችግር እንጂ በኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ላይ ብቻ የተመረገ የቁም ህልም አይደለም። ግልጽ ዓላማ ያላቸው አንድ በመቶ ብቻ የሚሆኑት ናቸው በዓለም ላይ። የኢኮኖሚ ስርዓታቸው አድጎ ጥሩ ለብሰው፣ በልተውና የሚፈልጉት ተሟልቶላቸው ይኖራሉ እንጂ፣ ግልጽ ዓላማ ያላቸው በአደጉት ሀገርም የጠቀስኩት ቁጥርን አይሞሉም። ወደኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ አንድ ፐርሰንት ቀርቶ ዜሮ ምናምን ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ከ80 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው ሕዝባችን ዛሬም አርሶ ነው የሚበላው። የተለየ ህልም ሊኖረው ይገባል የሚባለው አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርሶ ይበላል! አርብቶ ይኖራል! ተብሎ ቁጭ። እንዴ.......ይሄ ግዙፍ ሕዝብ አርሼ መብላት ነው ህልሜ ብሎ ከደመደመ ሀገርን የሚቀይረው ጉልበት ከየት ነው የሚመጣው? ስለዚህ ዋናው ፈጣሪ የሰጠንን አዕምሯችንን መጠቀም ትተን፣ መሬትና ህንፃዎች ያፈሩትን ነገሮች ላይ ሙጥኝ ብለን እንኖራለን እንጂ...... እውነተኛው ጉዞ መጀመሪያ ትምህርት ማግኘት፣ ቀጥሎ ልምድ መቅሰም፣ በመቀጠል የመሳሳቻ መድረክ ውስጥ መግባት፣ ቀጥሎ ሳይሳሳቱ መስራት፣ ከዚያም ለሀገር ትልቅ ነገር ፈጥሮና ለተረካቢ ትውልድ ልምድን እያካፈሉ መኖር!!.....በእርግጥ ብዙ ወጣቶች ለልምድ ትኩረት አይሰጡም! ዋጋውን አያውቁትም። ትክክለኛው ፎርሙላ ግን መጀመሪያ ልምድ ማግኘት ሲሆን፣ ልምዱ ገንዘቡን ካለበት ያመጣዋል፣ ገንዘቡን በአቋራጭ ካገኘን ግን ልምዱን ሳናገኝ ልንቀር ነው። ገንዘቡ ሲያልቅ እኛም ቁጭ ልንል ነው! ይሄን ፎርሙላ አናገላብጠው......መጀመሪያ እውቀት፣ ከዚያ ባወቅነው ነገር ከሚያውቁ ሰዎች ተጠግተን ልምድ መቅሰም፣ ከዚያ በራስ መንገድ እየተሳሳትን መቀጠል፣ ከዚያ ከአርባ አመት በኋላ ሙሉ በሙሉ ስህተትን አስወግዶ አንድ ህልም ላይ አተኩሮ መስራት፣ እስከ 50 አመትም በራስ አቅም መስራት፣ ልክ 51ኛ አመት ላይ ቻይናዊው ጃክ እንዳሉት....." ተተኪ ትውልድ ማፍራትና ልምዱን አስጨብጦ፣ 60 አመት ሲሞላን ዘና ብለን መፅሓፋችንን መፅሓፍ እና ውቅያኖስ ዳርቻና መንፈስን ከሚያድሱ የተፈጥሮ መስዕቦች ጋር ሄዶ መዝናናት!!......ይሄ ነው አካሄዱ። አሁን ገንዘብ ከልምድ እየቀደመ ሰው አላዋቂ ሆኖ የገዛ ገንዘቡ ገሎታል። ጫት ቤት ሄዶ፣ አልኮል ካለበት ሄዶ፣ ቁማር ቤት ሄዶ በአጠቃላይ ለህይወቱ ትርጉም ከሌላቸው እና አላስፈላጊ ከሆኑ ቦታዎች ሄዶ እየተሰቃየና እየተጎሳቆለ ነው። ምክንያቱም ገንዘቡን በሒደት አላገኘውም! በልምድ የተገኘ ገንዘብ አይደለማ!! በልምድ ያልተገኘ ገንዘብ ደግሞ ለራስም፣ ለማዕበረሰብም፣ ለሀገርም ጥቅም የሚሰጥ ነገር አይሰራበትም።
." በእንግሊዘኛ Bottom line thinking" የሚባል አባባል አለ። እያንዳንዱ የደመደመበት አስተሳሰብ አለ። የአብዛኛውን ማዕበረሰባችን የአኗኗር ዘይቤ ወረድ ብለን ማየት እንችላለን። ቁርጥ ሥጋ የሚሸጥባቸው ቤቶች ብንሄድ ጠጠር መጣያ ቦታ አናገኝም፣ ድራፍት ቤት ብትሄድ ብርጭቆ ይዞ የሚሻማው ስፍር ቁጥር የለውም። ተመልሰህ ላይብረሪ ብትሄድ ቤቱ ባዶ ሆኖ ታገኘዋለህ! ስንት ሰዎች ቁጭ ብለው እያነበቡ ነው አውቶብስ ውስጥ ፣ ታክሲ ውስጥ፣ ወረፋ የሚጠበቅባቸው የአገልግሎት ቦታዎች ብትል በጣም ጥቂት ሰዎች ነው የምታገኘው!!.....ይህቺ Bottom line thinking ማለት አብዛኛው ህብረተሰብ ልክ ነው ብሎ ድምዳሜ ላይ ከደረሰበት የተሳሳተ አስተሳሰብ ላይ ሥራ ካልሰራን አሁን የምንለው አመለካከት ላይ ፈፅሞ ለውጥ አናመጣም። አብዛኛው ሰው ሆዱን አስቀድሟል፣ የሆድ መቅደም የአስተሳሰብ ድርቀትን ያመጣል። አዕምሮ መቅደም ሲገባው ሆድ ይቀድማል! ብዙ ነገርን ሊሞላልን የሚችለው የአዕምሮ መሙላት እንጂ የሆድ መሙላት አይደለም። የሆድ መሙላት ግሳት ነው.......ለመንቀሳቀስ ነው የሚያገለግለው! ለመኖር ነው የሚያገለግለው!! የአዕምሮ መሙላት ግን ብስለት ነው፣ እውቀት ነው፣ ልምድ ነው! የነገን ችግር የሚፈታበት አስተሳሰብ መቅረፅ ነው። የመጀመሪያው የተሳሳተ አመለካከትና የአብዛኛው የታዳጊ ሀገሮች ችግር ሆድን ማስቀደም ነው። መሰረታዊ ነገር ነው ይሉታል አንዳንድ ሰዎች። መሰረታዊ የሆነውን ሆድን ራሱ ለመሙላት መጀመሪያ መሰረታዊ ያልሆነውን አዕምሮ መሙላት ነው ብዬ አስባለው

Comments

Popular posts from this blog

የአብዲሳ አጋ ¬ አስገራሚ ታሪክ – የኢትዮጵያ ጀግና !!!

የዐቢይ ንግግር ሰባት አዕማድ

ኑ ሀገሬን እናዋልዳት