Posts

Showing posts from 2018

ኑ ሀገሬን እናዋልዳት

አዋላጇ ጠፍታ ልጁም በእግሩ መጥቶ እናቲቱ ሞተች ልጅዬውም ሞቶ የሚል የልቅሶ ግጥም አለ። ነፍሰ ጡር እናት ስትወልድ ልጁ በእግሩ ከመጣ አደጋ ነው ይባላል። ጎበዝ አዋላጅ አግኝታ ልጁ በአናቱ እንዲመጣ ልታግዛት ይገባል። ያ ካልሆነ ግን ባልተስተካከለ መንገድ የመጣውን ልጅ ለመውለድ የምታምጠው እናት፣ ለረዥም ጊዜ በማማጧ የተነሣ ደክማ ለሞት ትዳረጋለች። ልጇም የመሞት ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል። መውለድ ደስታ የሚሆነው ልጁ በሰላም ተወልዶ፣ ለእናቱ ጤናና ደስታ ካመጣ ነው። መውለድ ካልተስተካከለ ማርገዝ ብቻውን ድካም ነው። ለዚህ ነው ነፍሰ ጡሮች በሕክምና እርዳታ ሲታገዙ ቆይተው፣ በሕክምና እርዳታ እንዲወልዱ የሚመከረው። ሀገር ለውጥን ልትወልድ የምትችለው የለውጥን ጽንስ በጤናማ መልኩ አርግዛ በጤናማ መልኩ እንድትወልድ የሚረዷትን ሐኪሞች ካገኘች ነው። ጽንሱ ጤናማ መሆኑን በየጊዜው የሚከታተሉ፤ ችግር ሲፈጠር ወዲያው መፍትሔ የሚሰጡ። ስትወልድም ልጁም እናቲቱም ጤንነታቸው በተጠበቀበት መንገድ እንድትወልድ የሚረዱ አዋላጅ ሐኪሞች ያስፈልጓታል። ይህ ሲጠፋ ልጁም እናቲቱም ለሞት ይዳረጋሉ። ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ለውጥን ፀንሳ ታውቃለች። ብዙ ጊዜ የማታገኘው ጎበዝ አዋላጅ ሐኪም ነው። በዚህ ምክንያትም ብዙ ጊዜ ልጇ ሞቶባታል። ያውም በእርሷም ላይ ከባድ አደጋ አድርሶ። ማኅፀኗን ጎድቷት ስለሚሄድ፣ ሌላ ልጅ ለመጸነስ ዘመናትን እንዲፈጅባት አድርጎ። የቅርቡ ታሪካችንን እንኳን ብንመለከተው፣የልጅ ኢያሱን ዘመን ፀንሳ ነበር። ነገር ግን ካለፉት ዘመናት በተለየ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ሂደት ባለቤት እንዲሆን ከዘመኑ በቀደመ ሐሳብ የተነሣውን ወጣቱ ንጉሥ ሐሳቡን የሚያዋልድለትና ፅንሱ በእግሩ መጥቶ እናቱንም ራሱንም እንዳይገድል የሚያደርግ ሐኪም አጥቶ፣ ሀገሪቱ ያንን ዕድል አመከነች...

ዶ/ር አብይ ንግግር ለምን ተወደደ?

Image
ታሪካዊ እንደሆነ የተነገረለት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ንግግር ባልተለመደ መልኩ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል አስደስቷል፡፡ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ፡፡ ምስጢሩ ምንድን ነው? ከንግግራቸውም በመነሳት ብዙዎች ለጠ/ሚኒስትሩ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን በጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ላይ ያላቸውን አስተያየት አሰባስቦ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡                “ስለ ኢትዮጵያና ስለ ወላጅ እናታቸው ሲናገሩ አንብቻለሁ”                   አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ (የኦሮሞ አባገዳዎች ም/ቤት ሰብሳቢ)     በእውነት ዶ/ር አብይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቀውን ንግግር ነው ያደረጉት፤ አንጀት የሚበላ ነው፡፡ የተራራቀውን ህዝባችንን የሚያቀራርብ ነው፡፡ ከአንድ መሪ የሚያስፈልገውም ይሄ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም የተጠማው ይህን አይነቱን ውስጥን የሚያለመልም፣ ተስፋ የሚሰጥ፣ ትህትና የተሞላበትን ንግግር ነበር፡፡ እኛም እንደ አባ ገዳና ሃገር ሽማግሌ ስንመኝ የነበረው፣ እንዲህ ሃገሩን ከፍ አድርጎ የሚጠራ መሪን ነው፡፡ ቋንቋችን ዥንጉርጉር ይሁን እንጂ ደማችን አንድ ነው ብዬ ደጋግሜ ተናግሬያለሁ፡፡  ከዚህ በኋላ የሚፈለገው የተናገሩትን ወደ ተግባር እንዲለውጡልን ነው፡፡ መናገሩ ብቻ ሳይሆን ዋናው ተግባሩ ነው፡፡ ወደ ተግባር እንደሚለውጡት ደግሞ እተማመናለሁ፡፡ ከአንዲት ኢትዮጵያ...

ድኻ ወርቅ አይግዛ

‹ድኻ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት› ይላሉ የምንዳዬ እናት አባዬ፡፡ ‹ምነው አባዬ ድኻ በመከራ የገዛውን ወርቅ እንዴት ይጥፋበት ይላሉ› ብለን ሞገትናቸው፡፡ ‹እይውልህ እኛ ሠፈር አራት ኪሎ አዲሴ የሚሏት አንዲት ጎረቤታችን ነበረች፡፡ ቁርስ፣ ምሳና እራት የተዘበራረቁባት፡፡ ለነገሩ ላለው ነው እንጂ ለሌለው ሰው ምግብ ስሙ ያው ምግብ ብቻ ነው፡፡ ምግብ - ቁርስ፣ ምሳ እራት የሚሆነው በሰዓቱ ስታገኘው ነው፡፡ በሰዓቱ ካላገኘኸው ያው ምግብ ብቻ ነው፡፡ ከድንጋይ ትፈልቅቀው፣ ከሳጥን ትስረቀው ሳናውቅ አንድ ቀን በድንገት አራት ኪሎ ወርቅ ቤት ሄዳ ወርቅ ገዛች ተብሎ ተወራ፡፡ የቡና ሴቶች ‹ግማሽ ግራም ወርቅ ገዝታ በከረጢት ቋጥራ አስቀመጠችው› ብለው ያሽሟጥጧታል፡፡  የገዛች ለት ምሽት እኛ ቤት ቡና ተጠርታ መጣችልህ፡፡ ሴቱ ሁሉ ግጥም ብሏል፡፡ ተርብ ተርቦቹ ደግሞ የዛን ቀን አንድም ሳይቀሩ ተለቃቅመው መጥተውልሃል፡፡ ገና ወደቤት ስትገባ ከሁላችን ለይታ ‹ወይዘሮ የወርቅ ውኃ ደኅና አመሹ› አትልልህም፡፡ አሁን በእርሷ ቤት ወርቅ መግዛቷን ልትነግረን እኮ ነው፡፡ ተያየንና ‹ኡኡቴ› ብልን ዝም አልን፡፡ ገና ከጠፈር ወንበሩ ላይ ሳትደላደል ‹እኔኮ በዚህ ዘመን ድኻ እንዴት ይኖራል፤ እኛስ እሺ› ብላ አረፈችው፡፡ ‹እናንተ እነማን ናችሁ› አለቻት እቴኑ በዓይኗ ቂጥ እያየቻት፡፡ ከምንም ሳትቆጥራት ‹ኧረ እንዴው ተውኝማ፣ ወርቅ እንደዚህ ሰማይ ይንካ› አለች ቆሎውን እየዘገነች፡፡ ‹እኛ ወርቅ ዘመን እንጂ ወርቅ ምን ያደርግልናል› አሏት እማማ ትጓደድ፡፡ ላምሮት ተናደደችና ‹ምን ዳር ዳር ትያለሽ፣ ወርቅ ገዝተሻል› አለችና አፈረጠችው፡፡ ሴቱ ሁሉ አንድ ጊዜ ቤቱን በሁካታ ሞላው፡፡ መቼም እርሷ አፍርጠው ናት፡፡   ሳቃችንን ሳንጨርስ ‹ቆ...

የዐቢይ ንግግር ሰባት አዕማድ

Image
የሀገሬ ሰው ‹ካልተናገረ አይታይ ብልሃቱ፣ ካልታረደ ዓይታይ ስባቱ› ይላል፡፡ ንግግር የሰው ልጅ ከተሰጡት የላቁ ጸጋዎች አንዱ ነው፡፡ ንግግር ሰዎችን ሊያግባባቸው፣ ወደ አንድነትና ኅብረት ሊያመጣቸው፣ ሊያከራክራቸውና ሊያወያያቸው ኃይል አለው፡፡ ከመሪዎች ከሚጠበቁ ነገሮች አንዱ ኃይል ያለው ንግግር ነው፡፡ ኃይል ያለው ንግግር በሚመርጣቸው ቃላት፣ በሚጠቀምበት ድምፀት፣ በሚያቀርባቸው አገላለጦች፣ በሚሰጣቸው ምሳሌዎች፣ በሚቀርብበት ተፋሰስ፣ በሚዋቀርበት አሰካክና በምጣኔው ይታወቃል፡፡ ሊደመጥ፣ ሊነበብ የሚችል፣ በሐሳቡ ባንስማማም በአቀራረቡ የሚማርከን፣ በዝርዝሩ ባንግባባም ሐሳቡ ግን የሚገባን፤ ባንወደውም የምናደንቀው ንግግር ከመሪዎች ይጠበቃል፡፡ ዐፄ ምኒልክ ለዐድዋ ጦርነት ሕዝቡን ለመጥራት ያወጁት ዐዋጅ ከዐዋጅነቱ ይልቅ የመሪ ጥሪ የሆነ ቃል አለው፡፡ በውስጡ ንጉሡንና ሕዝቡን የሚያቀራርብ፣ የሀገሪቱን ችግር የሚገልጥ፣ ከሕዝቡ የሚፈልጉትን የሚያሳይ፣ ሀገር ስትጠራው እምቢ ብሎ የቀረ የሚገጥመውን ዕጣ ፈንታ የሚያመላክት ቃል ነው፡፡ መላዋን ኢትዮጵያ ለአንድ ዓላማ ያሰለፈና ውጤቱን በዐድዋ ተራሮች ላይ ያሳየ ቃል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሀገር ምጥ ላይ በምትሆንበት ጊዜ የመሪዎች ንግግር ወይ ፈዋሽ ወይ አባባሽ ይሆናል፡፡ ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል እንዲሉ፡፡ አነጋገሩ የሚያግባባ፣ የሚጠራና የሚያቀራርብ ከሆነ ሕዝብን ለመፍትሔ የማሰለፍ ኃይል ይኖረዋል፡፡ ንግግሩ ብቻ ሳይሆን ንግግሩ የተዋቀረበት መዓዝን የመሪውን ጉዞ ካርታውን እንድናይ ያደርገናል፡፡ የዶክተር ዐቢይ አሕመድ ንግግር በንግግሩ ይዘት፣ ንግግሩ በተቀናበረባቸው ቃላት፣ ቃላቱ በተሰናሠሉበት አወቃቀር፣ ሐሳቡ በተገለጠባቸው ምሳሌዎች፣ ማሳያዎች፣ ጥቅሶች፤ ትኩረትና አጽንዖት በተሰጣቸው ...